

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የደረጃ አንድ (Level 1) የቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎች መስጠት መጀመሩን ተከትሎ፣ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ስር የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች ተግባራዊ የልምድ ልውውጥ እና ጉብኝት አደረጉ፡፡
የጉብኝቱ ዓላማ አዲሱን አሰራር ለማጠናከር እና በተግባር የተደገፈ ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል ግንዛቤን ለመፍጠር እንደሆነ ታውቋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ የትምህርት አመራሮች፣ መምህራን እና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
የስልጠና እና አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ዲን ወ/ሮ ሳራ አበበ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ይህ አይነቱ ጉብኝት በተማሪዎች ዘንድ ስለ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ያለውን አመለካከት ለመቀየር ትልቅ ፋይዳ አለዉ ብለዋል።
“ቴክኒክና ሙያ በተፈጥሮው ተግባራዊ ስልጠና የሚሰጥበት ዘርፍ ነው” ያሉ ሲሆን “እኛ እና እናንተ ተቀናጅተን ከሰራን በተማሪዎች አመለካከት ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንችላለን” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለየት የሚያደርገውን ዋና ጉዳይ ሲያብራሩ፤ በዘርፉ የሚሰጡ ስልጠናዎች ሰልጣኞች ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ በቀጥታ ከስራ ዓለም ጋር ማስተሳሰር ግዴታ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት የሁለተኛ ደረጃ መምህራን እና ሱፐርቫይዘሮች በተቋሙ የሚገኙ የተግባር ስልጠና መስጫ ክፍሎችን እና የተለያዩ ወርክሾፖችን በመጎብኘት በዘርፉ ስላለው የስልጠና ሂደት ተግባራዊ ልምድ መውሰዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
.