

በ2018 በጀት ዓመት አዋጭነታቸው የተረጋገጡ እና የማህበረሰቡን ችግር በተጨባጭ የሚያቃልሉ ቴክኖሎጅዎችን ለመቅዳትና ወደ ስራ ለማስገባት ያለመ የግምገማ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተካሄደ መሆኑ ተገለጸ።
በዚህ መድረክ ላይ የውስጥ ችግሮችን ለማቃለል ታቅደው የተዘጋጁ እንዲሁም ከኢንተርፕራይዞች ፍላጎት በመነሳት የተሰበሰቡ የቴክኖሎጂ ሃሳቦች አዋጭነታቸው እና ችግር ፈቺነታቸው እየተፈተሸ ይገኛል።
የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን ዶ/ር ቢንያም አወቀ እንደገለጹት የተጀመረው አሰራር የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው የማህበረሰቡን ችግሮች የሚያቃልሉ ቴክኖሎጅዎችን ለይቶ ወደ ምርት ወይም ወደ ስራ ከመገባቱ በፊት ባለድርሻ አካላት ሃሳባቸውን እንዲያጋሩ እና አስተያየት እንዲሰጡበት መደረጉ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ይህ አይነቱ ተሳትፎ በዘርፉ የላቁ እና ጥራት ያላቸው ቴክኖሎጅዎችን ለማበርከት የሚያስችል አቅምን የሚፈጥር ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የቴክኖሎጅ ልማት እና ኢንደስትሪ ኤክስቴንሽን ምክትል ዲን ወ/ሮ አስናቀች መንግስቱ የግምገማው ዋና ዓላማ ሲገልጹ በፕሮፖዛል ደረጃ የቀረቡ የቴክኖሎጅ ሃሳቦች በትክክል ችግር ፈቺ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ያለመ ሲሆን መድረኩ ከባለድርሻ አካላት የሚሰጡ ገንቢ አስተያየቶችን በመቀበል እና ግብአቶችን በማካተት፤ በቀጣይ በማህበረሰባችን ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ ቴክኖሎጅዎችን ለመስራት የሚያስችል መተማመንን ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
መድረኩ የታቀዱት ቴክኖሎጂዎች የኢንተርፕራይዞችን እና የማህበረሰቡን ቀጥተኛ ፍላጎት የመለሱ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።
.