Application Form የህይወት ክህሎት ስልጠና የወሰዱ ከ400 በላይ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ተመርቀዋል

የህይወት ክህሎት ስልጠና የወሰዱ ከ400 በላይ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ተመርቀዋል

12th January, 2026

የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን ወደ ስራ ዓለም ለማቀላቀል ያለመ የህይወት ክህሎትና የስራ ማፈላለግ ስልጠና ሲከታተሉ የቆዩ 413 ስራ ፈላጊ ወጣቶች በዛሬው እለት ተመርቀዋል። 

ስልጠናው ከክፍለ ከተማው ሁለት ወረዳዎች ለተውጣጡ ወጣቶች ላለፉት አስራ ሁለት ቀናት ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ወጣቶቹን በስነ-ልቦና እና በክህሎት በማብቃት ወደ ስራ ገበያው እንዲቀላቀሉ ለማስቻል እንደሆነ ተገልጿል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ም/ስራ አስፈጻሚ እና የስራ እና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አከበረኝ ወጋገን ወጣቶቹ ስልጠናውን በብቃት በማጠናቀቃቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ሰልጣኞች በቀጣይ በሚዘጋጅላቸው የስራ ልምምድ (Apprenticeship) ፕሮግራም እንደሚሳተፉ ገልጸው፣ በቅጥርም ይሁን በግል ስራ ፈጥሮ ለመሰማራት በሚያስችሉ አማራጮች ላይ ተገቢው ድጋፍ እንደሚመቻችላቸው ቃል ገብተዋል።

የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ዋና ዲን ዶ/ር ቢንያም አወቀ በበኩላቸው፤ ወጣቶቹ ላለፋት አስራ ሁለት ቀናት የወሰዱት መሰረታዊ ስልጠና ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ዶ/ር ቢንያም ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልእክት በወሰዳችሁት ስልጠና መሰረት ራሳችሁን እና ቤተሰቦቻችሁን እንድትደግፉ፣ የኢንደስትሪ ባህርያት መሬት ላይ እንዲወርዱ እና የሃገራችንን የልማት አቅጣጫ ማስቀጠል የሚያስችል አቅም እንደፈጠራችሁ አምናለሁ ሲሉ ተናግረዋል።

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ ለተመራቂዎቹ የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን፣ ወጣቶቹም የተፈጠረላቸውን እድል ተጠቅመው ወደ ስራ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸው ተመላክቷል።

.

Copyright © All rights reserved.

Created with