
በዛሬው ዕለት በተከናወነው የ"ወርቃማው ሰኞ" መርሃ ግብር፣ ይሉኝታ በግላዊ ህይወት፣ በስራ አካባቢ እና በማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ላይ ያተኮረ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል። በመድረኩ ላይ ሰነድ ያቀረቡት አቶ ምስጋናው መኩ እንደገለጹት፤ ይሉኝታ ግለሰቦች የራሳቸውን ፍላጎት ገትተው "ሰዎች ምን ይሉኛል?" በሚል ስጋት ሌሎችን ለማስደሰት የሚጥሩበት የስነ-ልቦና ጫና ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቅራቢው ገለጻ ይሉኝታ የሚያጠቃቸው ሰዎች ከሚጠበቅባቸው ኃላፊነት እና ግዴታ በላይ የሌሎችን ጉዳይ ለመፈጸም ብዙ ርቀት ይጓዛሉ። ይህ ድርጊት ግለሰቦች የራሳቸውን ስራና አጀንዳ ወደ ጎን በመተው፣ የራሳቸውን ምርጫና ፍላጎት ተጭነው ለሌሎች ቅድሚያ እንዲሰጡ እንደሚያደርጋቸው ተመልክቷል።
አቶ ምስጋናው ለይሉኝታ መንስኤ ይሆናሉ ያሏቸውን ነጥቦች እንደሚከተለው ዘርዝረዋል
ከመጠን በላይ የሌሎችን ሰዎች ተቀባይነትና ትኩረት ለማግኘት መሻት፤ በራስ መተማመን ማነስ፤ ስለ ራስ ጥሩነት የሚሰማን ስሜት በሌሎች አስተያየትና ማሞካሸት ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆን፤ የውስጥ መረጋጋት ማጣት እንሆኑ አንስተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የኮልፌ ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ ምክትል ዲን አቶ ምትኩ ሃንካሶ በበኩላቸው፤ ይሉኝታ የራስን ጥቅም አሳልፎ መስጠትና በህይወት ውስጥ ሚዛናዊነትን ማጣት መሆኑን በመግለጽ ሁሉም ሰው ራሱን ሊፈትሽ እንደሚገባ እና ከእንደዚህ አይነት አጉል ልምምዶች ተላቆ ህይወትን በምክንያታዊነትና በተገቢው መንገድ መምራት ለስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
.